የባንክ ካርድ ዓይነቶችን በሚገባ ያውቋቸዋል?

በቅድመ-ክፍያ፣ ዴቢት እና ክሬዲት ካርዶች መካከል ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶች

 

በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ካርዶችን ለግዢ፣ ለገንዘብ ወጪ፣ እንዲሁም ለኦንላይን ክፍያዎች መጠቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መጥቷል፡፡ የካርዶቹ ዓይነትና አገልግሎት እየሰፋ ከመምጣቱም በላይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መመሪያ ተከትሎ ከባንኮች በተጨማሪ ሌሎች የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ተቋማትም ካርዶችን ለደንበኞች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ፣ አሁንም ድረስ በርካታ ተጠቃሚዎች በክሬዲት (Credit)፣ ዴቢት (Debit) እና ቅድመ-ክፍያ (Prepaid) ካርዶች መካከል ያለውን መመሳሰልና መሠረታዊ ልዩነቶች በግልጽ ሲለዩ አይታይም፡፡

 

ይህ ብዥታ ሊፈጠር የቻለበት ዋናው ምክንያት ካርዶቹ በገጽታቸው እጅግ በጣም ተመሳሳይ በመሆናቸው ነው፡፡ ሁሉም ካርዶች በአብዛኛው የሚከተሉትን አካትተው ይዘዋል፡

    • የካርድ መለያ ቁጥር (PAN)

    • የተጠቃሚው ስም

    • አገልግሎቱ የሚያበቃበት ቀን (Expiry Date)
    • የካርድ ሰጪው ተቋምና የክፍያ አስተናጋጁ (እንደ ቪዛ ወይም ማስተርካርድ) አርማዎች
    • እንዲሁም በአዲሶቹ ካርዶች ላይ የንክኪ-አልባ (Contactless) ክፍያ ምልክት

 

ምንም እንኳን በገጽታቸው አንድ ዓይነት ቢመስሉም፣ ከጀርባ ባለው የፋይናንስ አሰራር ግን መሠረታዊ የሆነ ልዩነት አላቸው፡፡ የካርዶቹን ተፈጥሯዊ ልዩነት እንደሚከተለው በዝርዝር እንመልከት:-

 

 

1.⁠ ⁠ቅድመ-ክፍያ ካርድ (Prepaid Card)

 

የቅድመ-ክፍያ ካርድ ማለት ከባንክ ሒሳብ ጋር መገናኘት (Link መደረግ) ሳያስፈልገው፣ በቅድሚያ ገንዘብ ተጭኖበት በዲጂታል የክፍያ ዋሌት (Digital Wallet) አማካኝነት አገልግሎት የሚሰጥ የካርድ ዓይነት ነው፡፡ እነዚህ ካርዶች በአብዛኛው በቪዛ ወይም በማስተርካርድ ኔትዎርክ ስለሚደገፉ፣ ከሀገር ውስጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡

የቅድመ-ክፍያ ካርዶች ዋነኛ መለያቸው “በተጫነባቸው የገንዘብ መጠን ልክ ብቻ” ማገልገላቸው ነው፡፡ ገንዘቡ ሲያልቅ እንደገና እስኪጫንባቸው ድረስ ግብይት መፈጸም አይቻልም፡፡ በዋናነት በአራት ይከፈላሉ፡

 

የሥጦታ ካርዶች (Gift Cards)፡ በስጦታ መልክ ለወዳጅ ዘመድ የሚሰጡ ሲሆኑ፣ በውስጣቸው ያለው የገንዘብ መጠን ካለቀ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ መልሶ መጠቀም (Reload ማድረግ) አይቻልም፡፡

 

የችርቻሮ እና የሽልማት ካርዶች (Retail Prepaid Cards)፡ ነዳጅ አቅራቢዎች፣ አየር መንገዶች ወይም ሱፐር ማርኬቶች ከባንኮች ጋር በመተባበር የሚያዘጋጇቸው ናቸው፡፡ ደንበኞች ግብይት ሲፈጽሙ የሽልማት ነጥቦችን፣ የአየር ማይሎችን (Miles) ወይም የዋጋ ቅናሾችን እንዲያገኙ ያግዛሉ፡፡

 

የጉዞ ካርዶች (Travel Cards)፡ ወደ ውጭ ሀገር ለሚጓዙ ግለሰቦች ቪዛቸውና ትኬታቸው ታይቶ በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ተጭኖባቸው የሚሰጡ ናቸው፡፡ በሄዱበት ሀገር ለሆስፒታል፣ ለሱቆች እና ለኦንላይን ክፍያዎች ያገለግላሉ፡፡ ለምሳሌ የአቢሲንያ ባንክ የጉዞ ካርድ፣ ከተጫነበት የመጀመሪያ መጠን በተጨማሪ አስከ 3,000 የአሜሪካን ዶላር ድረስ ከሌላ አካል ሊቀበል የሚችልበት አሰራር አለው፡፡

 

ለዕለታዊ ግብይት የሚውሉ (General Purpose Cards)፡ ለማንኛውም ዓይነት የዕለት ተዕለት ወጪዎች የሚያገለግሉና ገንዘብ ሲያልቅባቸው ደጋግመው ሊሞሉ የሚችሉ (Reloadable) ናቸው፡፡ እነዚህ ካርዶች ወጪን ለመቆጣጠር (Budgeting) እጅግ ጠቃሚ ናቸው፤ ምክንያቱም ከተጫነው ገንዘብ ውጪ ማውጣት ስለማይቻል ከልክ ያለፈ ወጪን ይከላከላሉ፡፡

 

2.⁠ ⁠ዴቢት ካርድ (Debit Card)

 

ዴቢት ካርድ በአብዛኛው ከግል የቁጠባ ወይም ከተንቀሳቃሽ የባንክ ሒሳብዎ (Bank Account) ጋር በቀጥታ የተገናኘ (Linked) ነው፡፡ ይህ ካርድ በሒሳብዎ ውስጥ ያለዎትን የራስዎን ገንዘብ በቀላሉ ወጪ ለማድረግ፣ ግብይት ለመፈጸም እና ክፍያዎችን ለማከናወን የሚያስችለው ነው፡፡

 

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ፣ በዴቢት ካርድ በሒሳብዎ ውስጥ ካለው ገንዘብ በላይ ማውጣት አይቻልም፡፡ ሆኖም ወደፊት የባንክ አሰራሮች እያደጉ ሲመጡ፣ አንዳንድ የዴቢት ካርዶች ከ”ኦቨር ድራፍት” (Overdraft) አገልግሎት ጋር ተገናኝተው የራስዎ ገንዘብ ቢያልቅም የተወሰነ ተጨማሪ ገንዘብ ከባንኩ በጊዜያዊነት መጠቀም የሚችሉበት አሰራር ሊኖር ይችላል፡፡

 

 

3.⁠ ⁠ክሬዲት ካርድ (Credit Card)

 

ክሬዲት ካርድ በአጭር አገላለጽ “አሁን ገዝተው በኋላ የሚከፍሉበት” የብድር ካርድ ነው፡፡ በሒሳብዎ ውስጥ ገንዘብ ባይኖርዎትም፣ ባንኩ በፈቀደልዎ የብድር ጣሪያ (Credit Limit) ልክ የተለያዩ ግብይቶችን መፈጸም ይችላሉ፡፡

ጥቅሙ፡ ክሬዲት ካርድን በኃላፊነት ከተጠቀሙ እና ወርሃዊ ክፍያዎን በወቅቱ ከመለሱ፣ የብድር ታሪክዎን (Credit Score) ለማሳደግ ይረዳዎታል፡፡ ይህም ወደፊት ትልልቅ ብድሮችን ከባንክ ለማግኘት በር ይከፍታል፡፡

ጉዳቱ፡ ካርዱን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ መጠቀም እና አቅምን ያላገናዘበ ወጪ ማድረግ የብድር መከማቸትን፣ ተጨማሪ ወለድን፣ ብሎም ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስን (Debt Trap) ሊያስከትል ይችላል፡፡

 

 

ማጠቃለያ

 

የባንክ ካርዶች የዕለት ተዕለት የፋይናንስ እንቅስቃሴያችንን በማቅለል ረገድ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት መሠረታዊ ልዩነቶች በተጨማሪ፣ የካርድ ሰጪ ተቋማት ካርዶቹን እንደየደንበኞቻቸው ፍላጎትና አቅም በደረጃ (Standard, Gold, Platinum, Premium ወዘተ) ከፋፍለው ያቀርቧቸዋል፡፡ የእነዚህ ደረጃዎች ልዩነት በካርዶቹ ላይ በሚኖረው የግብይት ገደብ፣ በሚሰጡት ተጨማሪ ጥቅማጥቅሞች እና በአገልግሎት ክፍያቸው ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዚህ ካርድ ሲመርጡ የራስዎን የፋይናንስ ፍላጎትና የካርዱን ባህሪ በሚገባ ማገናዘብ ብልህነት ነው፡፡

Other Posts