የኤቲኤም (ATM) ካርድ ማጭበርበር ምንድነው?

በተለምዶ የኤቲኤም (ATM) ካርድ የምላቸው የዴቢት/ክሬዲት ካርዶች በኪሳችን ውስጥ ብዙ ጥሬ ገንዘብ የመያዝን አስፈላጊነት በማስቀረት ሕይወታችንን በእጅጉ አቅልለውልናል። ነገር ግን እነዚህን ካርዶች በጥንቃቄ ካልያዝናቸው ወይም ሚስጥራዊ ቁጥራችን ዘራፊዎች እጅ ከገባ፣ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የባንክ አካውንታችንን ወና ሊያደርጉት ይችላሉ። ይህ አደጋ “የካርድ ማጭበርበር/ዝርፊያ” (Card Fraud) ይባላል።

ይህ ወንጀል በአብዛኛው የሚፈጸመው ካርዳችን ሲጠፋ ወይም ሲሰረቅ፣ በተለይም ደግሞ ሚስጥራዊ ቁጥሩን (PIN) ከካርዱ ጋር አብረን አስቀምጠን ሌባው በቀላሉ ሲያገኘው ነው። እንዲሁም ሌቦች ቁጥራችንን በድብቅ አይተው ካርዱን በፍጥነት በመስረቅ እኛ ባንክ ደውለን ካርዱን ሳናሳግደው (Block ሳናደርገው) በፊት በፍጥነት ብር ያወጡበታል።

አጭበርባሪዎች ይህንን ወንጀል እንዴት ይፈጸማሉ?

  1. ካርዱን በእጅ ማስገባት፦ ካርዱ ከኪስዎ በስርቆት ሊወሰድ፣ ከቦርሳዎ ጋር አብሮ ቢሰረቅ፣ ቢጠፋ ወይም ረስተውት ከሄዱ
  2. ሚስጥራዊ ቁጥሩን (PIN) ማግኘት፦ ብዙ ሰዎች የኤቲኤም ቁጥራቸውን እንዳይረሱት በማሰብ በወረቀት ጽፈው ከካርዱ ጋር አብረው ያስቀምጣሉ፤ ይህ ደግሞ ለሌባው ትልቅ ሲሳይ ነው። በተጨማሪም በኤቲኤም ማሽን ላይ ብር ሲያወጡ ሌባው ከበስተጀርባዎ ቆሞ ቁጥርዎን በጥንቃቄ ሊያይ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሆን ብለው የእርስዎን ትኩረት በመስረቅ ካርዱንና ቁጥሩን ይወስዳሉ።
  3. በፍጥነት ገንዘብ ማውጣት፦ ሌባው ካርዱንና ቁጥሩን እንዳገኘ፣ እርስዎ ካርዱ መጥፋቱን አውቀው እስኪያሳግዱ ድረስ ባሉት ጥቂት ሰዓታት ወይም ደቂቃዎች ውስጥ በፍጥነት ብር ያወጣል ወይም ግዢዎችን ይፈጽማል። በዚህ አደጋ ውስጥ እያንዳንዱ የዘገዩበት ሰዓት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያሳጣዎታል።

ሊያጠራጥሮት የሚገቡ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች

  • ካርዱ ድንገት ከኪስዎ ወይም ከቦርሳዎ መጥፋቱ።
  • እርስዎ ያላደረጉት የገንዘብ ወጪ ወይም ግዢ በስልክዎ መልዕክት (SMS) ሲደርስዎት።
  • በኤቲኤም (ATM) ማሽን ላይ ብር ሲያወጡ ወይም በካርድዎ ከፍያ ሲፈጽሙ አንድ ሰው በጣም ተቀራርቦዎት ከቆመ ወይም “ላግዝዎት” በማለት ጣልቃ ለመግባት ከሞከረ።

ራሳችንን እንዴት እንጠብቅ?

  • ሚስጥራዊ ቁጥሩን (PIN) በጭንቅላት መያዝ፦ የኤቲኤም ቁጥርዎን በፍጹም ከካርዱ ጋር አብረው አይጻፉ። ባንክ ቁጥሩን በወረቀት በፖስታ ሲሰጥዎት ወዲያውኑ በጭንቅላትዎ ይሸምድዱት ወይም ሰውፈጽሞ ሊያገኘው የማይችለው ቦታ ያስቀምጡት።
  • ቁልፎቹን መጋረድ፦ በኤቲኤም ማሽን ወይም በሱቆች ክፍያ በሚፈጽሙበት ማሽን ላይ ቁጥርዎን ሲያስገቡ ሁልጊዜ በሌላኛው እጅዎ ቁልፎቹን በጥንቃቄ ይጋርዱ
  • በፍጥነት ማመልከት፦ የባንክዎን ካርድ ማሳገጃ (Block ማድረጊያ) ስልክ ቁጥር ወይም አጭር ቁጥር በስልክዎ ላይ አስቀድመው መዝግበው ይያዙ። ካርዱ መጥፋቱን ወይም መሰረቁን ካወቁ በዕለታት ሳይሆን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በፍጥነት ደውለው ወይም ባቅራቢያዎ ወዳለ ቅርንጫፍ በመሄድ ያሳግዱት።
  • የአጭር የጽሑፍ (SMS) መልዕክት ማብራትና መከታተል፦ በካርድዎ ላይ የሚደረጉ ማናቸውንም ግብይቶች ወዲያውኑ በስልክዎ ላይ በጽሑፍ መልዕክት (SMS Alert) የማይደርስዎት ከሆነ ባንክዎን ያነጋግሩ። በተጨማሪም መልክቶችን በወቅቱ በመከታተል እርስዎ የፈጸሙት ትክክለኛ ግብይት መሆኑን ያረጋግጡ

Other Posts