ዋትስአፕዎ በድምፅ መልዕክት (Voicemail) ሀኪንግ እንዳይሰረቅ እንዴት ይከላከላሉ

በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን በተለያዩ የሀኪንግ ዘዴዎች አካውንታቸው ሀክ ሲደረግ እየተስተዋለ ነው። በዚህ ማብራሪያ የምንመለከተው ድምፅ መልዕክት (Voicemail) ሀኪንግ ነው። ይህ ዘዴ ባብዛኛው በውጭ ሀገር ስልክ ቁጥሮች በመደወል የዋትስአፕ አካውንትን ለመጥለፍ እና ከዛም በተጠቃሚው ስም ለቤተሰብ ወይም ለጓደኛ መልዕክት በመላክ ገንዘብ እንዲያስገቡላቸው  ለመጠየቅ ያለመ ነው።

ማጭበርበሩ የሚፈጠርበትን አጋጣሚ እንመልከት 

በመጀምሪያ አጭበርባሪው በእርስዎ ስልክ ቁጥር ዋትስአፕ ለመክፈት ይሞክራል።

ዋትስአፕ የማረጋገጫ ኮድ (OTP) በድምፅ ጥሪ እንዲልክ ይመርጣል። ልክ ዋትስአፕ ሊደውልልዎ ሲል፣ አጭበርባሪው ወደ እርስዎ ስልክ በመደወል መስመርዎን “ቢዚ” ያደርገዋል። መስመርዎ ቢዚ ስለሆነ፣ የዋትስአፕ አውቶማቲክ ጥሪ ሚስጥራዊ ኮዱን በድምፅ መልዕክት ሳጥንዎ (Voicemail) ላይ ያስቀምጠዋል።

ብዙ ሰዎች ለድምፅ መልዕክት የሚጠቀሙት የይለፍ ቃል “ዲፋቱን” ወይም ተገማች ስለሆነ፣ አጭበርባሪው በቀላሉ ሰብሮ በመግባት ኮዱን ይወስዳል፤ ከዚያም አካውንትዎን ይቆጣጠራል።

እንዲህ አይነቱን ማጭበርበት እንዴት መከላከል ይቻላል?

የድምፅ መልዕክት ሳጥንዎን (Voicemail) ሚስጥራዎ ቁጥር PIN ማጠናከር: የሚጠቀሙት PIN “ዲፎልት” ወይም በቀላሉ ተገማች ከሆነ አጭበርባሪዎች በቀላሉ የእርስዎን ድምጽ ሳጥን መስማት ይችላሉ። ወደ 824 በመደወል የድምፅ መልዕክት ሳጥን Setting ውስጥ በመግባት የይለፍ ቃልዎን ይቀይሩ ። እንደ 1234፣ 0000፣ ወይም የስልክ ቁጥርዎ የመጨረሻ ዲጂቶች ያሉ ቀላል ቁጥሮችን አይጠቀሙ።

Two-Step Verification (2SV) መጠቀም: ይህ ዋነኛውና ጠንካራው መከላከያ መንገድ ነው ። ሃከሩ ወይም አጭበርባሪው የማረጋገጫ ኮዱን(OTP) ቢያገኝ እንኳን፣ እርስዎ ያዘጋጁትን ይህንን ሚስጥራዊ ቁጥር (PIN) ካላወቀ ወደ አክውንትዎ መግባት አይችልም ። ዋትሳፕ ላይ ወደ Settings > Account > Two-step verification በመሄድ “Turn On” የሚለውን ይጫኑ ። ጠንካራ PIN  ያስገቡ፤ የRecovery Email ይጨምሩበት። 2SV ባጠቃላይ አብዛኛውን ሀክ የመደረግ አጋጣሚዎችን ለመከላከል ይጠቅማል።  

አጠራጣሪ ጥሪዎችን መጠንቀቅ፡ የዋትስአፕ “Login Code” ወይም የማረጋገጫ መልዕክት በስልክዎ ላይ እየመጣ ባለው ሰዓት  ከማያውቁት ሰው  ወይም ከውጭ ሀገር ቁጥር ሲደወልልዎ ሳያረጋግጡ አያንሱ።  መስመርዎ “ቢዚ” እንዲሆን አያድርጉ ስልኩን አለማንሳት ወይም መዝጋት ይሻላል። በአጠቃላይ ፈጽሞ ከማያውቁት ወይ ከማይጠብቁት ቁጥር ስልክ ሲደወል መጠራጠር ጠቃሚ ነው። 

ዋትስአፕዎ ሀክ ሲደረግ ምን ማድረግ አለብዎት?

ድንገት የአክውንትዎን አክሰስ ቢያጡ እና በስምዎ  “ቶሎ ይሄን ያህል ብር ወደዚህ አካውንት ላክልኝ አስቸኳይ ነው” የሚል ይዘት ያለው መልዕክት እየተላከ እንደሆነ ከሰሙ፡- ወዳጅ ዘመድዎን ለማንም ሰው ገንዘብ እንዳይልኩ ወዲያውኑ ያስጠንቅቁ ።

ወዲያውኑ መልሰው ወደአካውንትዎ ለመግባት ይሞክሩ (Re-register Immediately)። በኤስኤምኤስ (SMS) የሚላክልዎትን አዲስ ኮድ ሲያስገቡ፣ በሌሎች ስልኮች ወይም ኮምፒውተሮች ላይ ተከፍተው የነበሩ የእርስዎ የዋትስአፕ አካውንቶች በሙሉ በራሳቸው ይዘጋሉ:: 

ይህን ሲያደርጉ የ two-step verification PIN ቁጥር እንዲያስገቡ ሊጠየቁ ይችላሉ። የፒን ቁጥሩን የማያውቁት ከሆነ፣ ምናልባት አካውንቶን ሀክ ያደረገው ሰው የራሱን ፒን ቁጥር አስገብቶ ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነት ሁኔታ ካጋጠመዎት 7 ቀናት ጠብቀው እንደገና ይሞክሩ። የፒን ቁጥሩን ቢያውቁም ባያውቁም፣ ባለ 6 አሃዝ የኤስኤምኤስ ኮዱን እንዳስገቡ የእርስዎን አካውንት እየተጠቀመ ያለ ማንኛውም ሰው ወዲያውኑ ከአካውንቱ ይወጣል።

ሪፖርት ያድርጉ፡ አጭበርባሪው የላከውን የባንክ ሂሳብ ቁጥር (ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወይም ሌላ የባንክ አካውንት) ለባንኩ እና ለፖሊስ በማሳወቅ ይሞክሩ። ባንኮች እና የሚመለከታቸው አካላት እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን የማስተናገድ ፍላሆት ላይታይባቸው ቢችልም ፣ እርስዎ ግን የእርስዎን ድርሻ ለመወጣት የተቻለዎትን ሁሉ ያድርጉ።

Other Posts