ቴሌግራም፣ ዋትስአፕ ወይም ፌስቡክ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን እና የንግድ ሥራችን ዋነኛ አካል ናቸው። ነገር ግን እነዚህን መተግበሪያዎች ተጠቅመው የቅርብ ሰዎቻችንን በመምሰል ገንዘብ የሚዘርፉ አጭበርባሪዎች በብዛት እየተከሰቱ ነው። ይህንን ማጭበርበር በእንግሊዘኛው “የአካውንት መጥለፍ” (Hacked Account) ይባላል።
ይህ ዓይነቱ ማጭበርበር እንዴት እንደሚሰራ፣ ምልክቶቹን እና ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን በቀላሉ እንይ።
ይህ ማጭበርበር ምንድን ነው? እንዴትስ ይፈጸማል?
አጭበርባሪዎች የሰዎችን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት በተለያየ መንገድ ከሰረቁ በኋላ፣ በእነሱ ስም በኮንታክት ዝርዝራቸው ውስጥ ላሉ ጓደኞች እና ዘመዶች መልዕክት ይልካሉ።
ክስተቱ የሚፈጸመው በሚከተለው መልኩ ነው፦
- ኮድ ማታለል፦ አጭበርባሪው በተለያየ መንገድ (ለምሳሌ “ሊንክ ንካ” በማለት ወይም “ፎቶሽን እዚህ ቦታ አገኘሁት” በማለት) የስልክዎን ማረጋገጫ ኮድ (Verification Code) እንዲሰጡት ያደርጋል።
- አካውንቱን መቆጣጠር፦ ኮዱን ካገኘ በኋላ እርስዎን ከአካውንቱ አስወጥቶ (Lock out) ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠረዋል።
- ገንዘብ መጠየቅ፦ በአካውንቱ ውስጥ ለሚገኙ ኮንታክቶች “አደጋ ደርሶብኝ ነው”፣ “ገንዘብ ለመላክ ተቸግሬ ነው” ወይም “አስቸኳይ የሚከፈል ዕቃ ገዝቼ ነው” በማለት የገንዘብ እርዳታ ይጠይቃል።
- ገንዘቡን ማሸሽ፦ ወዳጆችዎ የእርስዎ መስሏቸው ወደተሰጣቸው የባንክ አካውንት ወይም የሞባይል ሂሳብ (Mobile money account) ገንዘብ እንደላኩ፣ አጭበርባሪው ወዲያውኑ ገንዘቡን ወደ ሌላ አካውንት በማዛወር ይሰወራል።
ልናስተውላቸው የሚገቡ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች
አንድ የቅርብ ጓደኛ ወይም ዘመድ በፈጣን መልዕክት (Chat) ገንዘብ ሲጠይቅዎት የሚከተሉትን ነገሮች ካዩ ወዲያውኑ ይጠራጠሩ፦
- በስልክ ከመደወል ይልቅ በጽሑፍ ብቻ መለመን፦ ሁልጊዜ በስልክ የሚያገኙት ሰው ድንገት በጽሑፍ ብቻ “ገንዘብ ላክልኝ” ካለ።
- መልዕክቱ በጣም አስቸኳይ እና ሚስጥራዊ መሆን፦ “አሁኑኑ ካልላክሽልኝ” የሚሉ አይነት ቃላት ሲበዛበት።
- የባንክ አካውንቱ ስም አለመመሳሰል፦ ገንዘብ እንዲላክበት የተሰጠው የባንክ አካውንት ወይም የሞባይል ዋሌት ስም ከሚያውቁት ሰው ስም ጋር የማይገጥም ከሆነ።
- የማረጋገጫ ኮድ መጠየቅ፦ ማንኛውም ሰው ወደ ስልክዎ የተላከ የይለፍ ቃል ወይም ኮድ እንዲልኩለት ከጠየቀዎት።
ራሳችንን እንዴት እንጠብቅ?
- ኮድ ለሰዎች አለመስጠት፦ ምንም አይነት የጽሑፍ ማረጋገጫ ኮድ ለጓደኛም ቢሆን በፍጹም አያጋሩ።
- ባለ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫ (Two-Step Verification) ማብራት፦ በቴሌግራም፣ ዋትስአፕ እንዲሁም ሌሎች የመልእክት መላላኪያ ያ መገልገያዎች ላይ በሙሉ ሴቲንግ (Settings) ውስጥ በመግባት ባለ ሁለት ደረጃ ማረጋገጫ የይለፍ ቃል ያስገቡ። ይህ ሲሆን ኮዱ ቢሰረቅ እንኳ አጭበርባሪው አካውንትዎን መክፈት አይችልም።
- ደውለው ማረጋገጥ፦ አንድ ጓደኛዎ በጽሑፍ መልዕክት ገንዘብ ሲጠይቅዎት፣ መጀመሪያ ወደ ትክክለኛ ስልኩ ደውለው እሱ መሆኑን በድምፅ ያረጋግጡ።
- አካውንትዎ ከተጠለፈ፦ የእርስዎ አካውንት ከተጠለፈ፣ በፍጥነት በሌላ መንገድ (በስልክ ጥሪ ወይም በሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች) ለጓደኞችዎ መልዕክት በመላክ “አካውንቴ ተጠልፏል፣ ገንዘብ እንዳትልኩ” ብለው ያስጠንቅቁ።

