የማንነት እና የባንክ አካውንት ጠለፋ

በቴክኖሎጂው ዓለም ውስጥ ከአጠቃላይ የማጭበርበር ዓይነቶች ሁሉ እጅግ አስፈሪው ሌባው የእርስዎን ማንነት ሙሉ በሙሉ ተክቶ የሚንቀሳቀስበት መንገድ ነው። ይህ በፋይናንስ ቋንቋ “የአካውንት ወይም የማንነት ጠለፋ” (Account or Identity Takeover) ይባላል።

ይህ የዝርፊያ አይነት በሀገራችን የተለመደ የዝርፊያ አይነት ባይሆንም የፋይናስ ዘርፉ እየተወሳሰበ ሲመጣ እየተስፋፋ የሚሄድ በመሆኑ ካሁኑ መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው።

በዚህ ማጭበርበር ወቅት አጭበርባሪው የእርስዎን የሞባይል ወይም የኢንተርኔት ባንክ መተግበሪያ ሰብሮ በመግባት፣ የስልክ ቁጥርዎን ወደ ሌላ ሲም ካርድ በማዛወር ወይም የእርስዎን ማንነት መግለጫ ሰነዶች (እንደ መታወቂያ) በመጠቀም እርስዎ የማያውቁትን የባንክ አካውንት ከፍቶ ይንቀሳቀሳል። ባጭሩ ሌባው እርስዎን ሆኖ ይገኛል?

ይህ ማጭበርበር እንዴት ይፈጸማል?

አጭበርባሪዎች ይህንን ወንጀል ለመፈጸም የሚከተሉትን የሚከተሉትንዋና ዋና ደረጃዎች ይጠቀማሉ፦

  1. መረጃዎችን መስረቅ፦ በመጀመሪያ የእርስዎን የባንክ መግቢያ ስም እና የይለፍ ቃል በተለያዩ የማታለያ ሊንኮች (Phishing)፣ አደገኛ ቫይረሶች (Malware) ወይም በስነ-ልቦና ማታለል (Social Engineering) አማካኝነት ይሰርቃሉ።
  2. የሲም ካርድ ቅያሬ (SIM Swap)፦ አጭበርባሪው የእርስዎን የግል መረጃ በመጠቀም ወደ ቴሌኮም ድርጅት በመሄድ “ስልኬ ጠፋብኝ” በሚል ሰበብ የእርስዎን ቁጥር ወደ አዲስ ሲም ካርድ እንዲዛወርለት ያደርጋል። በዚህ ጊዜ የእርስዎ ስልክ ኔትወርክ ሙሉ በሙሉ ሲቋረጥ፣ ወደ እርስዎ መምጣት የነበረባቸው የባንክ ማረጋገጫ ኮዶች (OTPs) በሙሉ ወደ አጭበርባሪው ስልክ ይሄዳሉ።
  3. ገንዘብ ማዘዋወር፦ የእርስዎ የባንክ መግቢያ እና የማረጋገጫ ኮዱ በእጃቸው ከገባ በኋላ፣ ወደ አካውንትዎ በመግባት ገንዘብ ያዛውራሉ።
  4. በማንነትዎ አካውንት መክፈት፦ የእርስዎን የታደሰ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ፎቶ ኮፒ ካገኙ፣ በእርስዎ ስም አዳዲስ የባንክ አካውንቶችን በመክፈት ለሌላ የወንጀልና የማጭበርበሪያ ተግባር መፈጸሚያነት ይጠቀሙበታል።

ሊያጠራጥርዎት የሚገቡ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች

የሚከተሉትን ያልተለመዱ ክስተቶች ካዩ ማንነትዎ ወይም አካውንትዎ የመጠለፍ አደጋ ላይ መሆኑን በፍጥነት ይረዱ፦

  • የስልክ ኔትወርክ ድንገት መጥፋት፦ ስልክዎ ያለ ምንም ምክንያት ድንገት የአገልግሎት መስመር (Network) ካጣ።
  • ያልጠየቁት የማረጋገጫ ኮድ (OTP) መምጣት፦ እርስዎ ምንም አይነት የባንክ ግብይት ሳያደርጉ ወይም ለመግባት ሳይሞክሩ የይለፍ ቃል መቀየሪያ ወይም የውስጥ ኮድ መልዕክቶች ወድ ስልክዎ ሲመጡ።
  • የማያውቁት የገንዘብ ዝውውር፦ በባንክ ሂሳብዎ ላይ እርስዎ ፈጽሞ ያላደረጉት የወጪ ግብይት ወይም የማያውቁት ተቀባይ ስም ተመዝግቦ ሲያገኙ።
  • ያልከፈቱት አካውንት ጥሪዎች፦ እርስዎ ፈጽሞ ካልሄዱበት ባንክ ወይም የብድር ተቋም ስለተመዘገበ ዕዳ ወይም አካውንት የስልክ ጥሪ ወይም ደብዳቤ ሲደርስዎት።

ራሳችንን እንዴት እንጠብቅ?

  • ጠንካራ የይለፍ ቃል መጠቀም፣፦ ለባንክ አካውንቶችዎ በቀላሉ የማይገመቱ ጠንካራ የይለፍ ቃላትን ይጠቀሙ።
  • በጽሑፍ መልዕክት ማሳሰቢያዎችን መከታታል፡ በማንኛውም ሰዓት በባንክዎ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ወዲያውኑ በጽሑፍ መልዕክት (SMS Alert) የሚያስውቆእኦት ስለሆነ የሚደርስዎትን የጽሑፍ መልዕክት ችላ አለማለት።
  • ኔትወርክ ሲጠፋ በፍጥነት እርምጃ መውሰድ፦ ስልክዎ ያለ ምንም ምክንያት ድንገት አገልግሎት ካቆመ፣ ሳይዘገዩ ወዲያውኑ ወደ ቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎ በመሄድ ያመልክቱ። ጉዳዩ የሲስተም ችግር ካልሆነ ወዲያውኑ ባንክዎ አካውንትዎ ለጊዜው እንዲታገድ ያድርጉ።
  • የማያውቁትን (አስተማማኝ ያልሆነ) መተግበሪያ (Apps) አለመጫን፦ ማንኛውም በስልክ የደወለልዎ ሰው “አካውንትዎን ለማስተካከል ነው” በሚል ሰበብ እንዲጭኑት የሚነግርዎትን ማናቸውንም መተግበሪያዎች በፍጹም በስልክዎ ላይ አይጫኑ።
  • የመታወቂያ ፎቶዎችን በጥንቃቄ መያዝ፦ የነዋሪነት መታወቂያ፣ ፓስፖርት ወይም የመንጃ ፈቃድ ፎቶዎችን በሶሻል ሚዲያ ላይ በፍጹም አያጋሩ። በጽሑፍ መልዕክትም ለሰዎች ሲልኩም ጥንቃቄ ያድርጉ።

Other Posts