ገንዘብ በስህተት የተላከ በማስመሰል የሚደረግ የማጭበርበር ዘዴ

በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሞባይል ባንኪንግ እና የዲጂታል የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቶችን ይጠቀማሉ። ይህንን ተከትሎ አጭበርባሪዎች “በስህተት ገንዘብ ወይም አየር ሰዓት ልኬብህ ነው፣ እባክህ መልስልኝ” በማለት የሰዎችን ደግነት ተጠቅመው ገንዘብ የሚዘርፉበት ዘዴ በስፋት እየተለመደ መጥቷል።

ይህ ማጭበርበር ምንድን ነው? እንዴትስ ይፈጸማል?

አጭበርባሪው ገንዘብ ወይም የሞባይል አየር ሰዓት በስህተት እንደላከላችሁ አስመስሎ በመማጸን፣ የእናንተ የሆነውን ገንዘብ እንድትልኩለት የሚያደርጉበት መንገድ ነው።

ሂደቱ የሚፈጸመው በሚከተለው መልኩ ነው፦

  1. የሐሰት መልዕክት (Fake SMS)፦ ልክ ከባንክ ወይም ከቴሌኮም እንደተላከ የሚያስመስል የሐሰት የገንዘብ ገቢ መልዕክት (SMS) ወደ ስልክዎ ይላካል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ከተሰረቀ ሌላ አካውንት ላይ እውነተኛ ትንሽ ገንዘብ ሊልኩላችሁ ይችላሉ።
  2. የልመና ስልክ ጥሪ፦ መልዕክቱ እንደደረሰዎት ወዲያውኑ ስልክ ይደወልልዎታል። ደዋዩ በጣም በተጨነቀ እና በሚያዘንን ድምፅ “የመጨረሻ ገንዘቤ ነበረች፣ እባክሽ መልሽልኝ” በማለት ይማጸናል።
  3. የራስን ገንዘብ ማጣት፦ እርስዎም በየዋህነት በእውነት ገንዘብ የገባልዎት መስሎዎት ከራስዎ ሂሳብ ላይ ገንዘቡን ይመልሳሉ። ነገር ግን ዋናው የገባው ማረጋገጫ የሐሰት መልዕክት ነው፣ ወይም ደግሞ የተሰረቀ አካውንት ስለሆነ ባንኩ በኋላ ላይ ያነሳዋል (Reverse ያደርገዋል)። በዚህ ጊዜ የእርስዎን እውነተኛ ገንዘብ አጭበርባሪው ወስዶባችኋል ማለት ነው።
  4. የአየር ሰዓት ማጭበርበር፦ በተመሳሳይ መልኩ “በስህተት ካርድ ሞልቼልህ ነው ወይም የኢንተርኔት ፓኬጅ ልኬልሽ ነውና መልሽልኝ” በማለት የሚጠይቁበትም ዘዴ አለ።

ልናስተውላቸው የሚገቡ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች

የተሳሳተ ዝውውር አጋጥሞኛል የሚል ሰው ሲያጋጥማችሁ የሚከተሉትን ምልክቶች ልብ በሉ፦

  • የሒሳብ አለመመሳሰል፦ የደረሳችሁ የጽሑፍ መልዕክት (SMS) እና በባንክ መተግበሪያችሁ (App) ወይም በ*ቁጥር# ገብታችሁ የምታዩት ትክክለኛ የቀሪ ሂሳብ መጠን የማይመሳሰል ከሆነ።
  • ከመጠን በላይ መቸኮል እና ማጣደፍ፦ ሰውየው እንድታስቡ ወይም ሂሳባችሁን እንድታረጋግጡ ጊዜ ሳይሰጣችሁ ሲያጨናንቃችሁ።
  • ወደ ሌላ አካውንት እንድትልኩ መጠየቅ፦ “ገንዘቡ የገባው ከዚህ ስልክ ቢሆንም፣ ስትመልሱልኝ ግን በዚህ በሌላ ቁጥር/አካውንት ላኩልኝ” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ።

ራሳችንን እንዴት እንጠብቅ?

  • ትክክለኛ ሂሳብዎን ያረጋግጡ፦ ወደ ስልክዎ የመጣውን የጽሑፍ መልዕክት (SMS) ብቻ በማየት አይታመኑ። ሁልጊዜ ወደ ባንክ መተግበሪያዎ (App) በመግባት ወይም የአገልግሎቱን አጭር ቁጥር በመጠቀም ትክክለኛ የገንዘብ መጠን መሆኑን ያረጋግጡ።
  • ለባንክ ወይም ለአገልግሎት ሰጪው እንዲደውሉ ይንገሯቸው፦ በእውነት በስህተት የላከ ሰው ከሆነ፣ ወደ ባንክ ወይም ወደ ደንበኞች አገልግሎት (ለምሳሌ ቴሌብር) ደውሎ ማመልከት ይችላል። ተቋማቱ ራሳቸው ዝውውሩን በሕጋዊ መንገድ የማስተካከል (Reverse የማድረግ) አካሄድ አላቸው።
  • በራሳችሁ ገንዘብ አትመልሱ፦ በስህተት የገባ ገንዘብ ካለ፣ በራሳችሁ ውሳኔ ተመላሽ ከማድረግ ይቆጠቡ። ለፋይናንስ ተቋሙ ማመልከት ሁነኛ አማራጭ ነው። በተለይም ደግሞ ወደ ሌላ የተለየ የባንክ አካውንት ወይም ስልክ ቁጥር በፍጹም ገንዘብ አይላኩ።

Other Posts