ወደ ኢንቨስትመንት ዓለም ለመግባት እና እንደ አክሲዮን (Shares)፣ ቦንድ (Bonds) እና የግምጃ ቤት ሰነዶች (Treasury Bills) ያሉ የፋይናንስ መዋዕለ ንዋዮችን ለመግዛት ሲያስቡ መጀመሪያ የሚያስፈልግዎት ነገር የብሮክሬጅ አካውንት (Brokerage Account) ነው።
ይህ አካውንት አዘውትረን ከምንጠቀምበት መደበኛ የባንክ አካውንት የተለየ ነው። መደበኛ የባንክ አካውንት ገንዘብ ለማስቀመጥ እና ለማስተላለፍ ብቻ የሚያገለግል ሲሆን፣ የብሮክሬጅ አካውንት ግን በሃገራችን በተጀመረው የካፒታል ማርኬት ውስጥ በመሳተፍ የድርጅቶች ወይም የተለያዩ የፋይናንስ መዋዕለ ንዋዮችን ባለቤት እንዲሆኑ በር የሚከፍትልዎት የኢንቨስትመንት ሂሳብ ነው።
ለምን ሕጋዊ ብሮከር ያስፈልገናል?
ማንኛውም ሰው በግሉ ወደ ገበያው ሄዶ አክሲዮን መግዛት ወይም መሸጥ አይችልም። ይህንን ለማድረግ በሕግ እውቅና እና ፈቃድ ያላቸው የገበያ አገናኞች ወይም ብሮከሮች (Brokers) ያስፈልጉናል።
አንድ ሕጋዊ ብሮከር የሚከተሉትን ነገሮች ያግዝዎታል፦
- የኢንቨስትመንት አካውንትዎን ይከፍታል፣ ያረጋግጣል።
- የእርስዎን የግዢ እና የሽያጭ ትዕዛዞች በገበያው ላይ ይፈጽማል።
- አዳዲስ አክሲዮኖች ለሕዝብ ሲቀርቡ (Public Offerings) እንዲሳተፉ ያደርጋል።
- የክፍያ እና የባለቤትነት ማስተላለፍ ሂደቶችን በሕጋዊ መንገድ ያከናውናል።
- የኢንቨስትመንትዎን የሀብት መዝገብ በጥንቃቄ ይይዛል።
- ስለ ገበያው ክፍያዎች እና አሰራሮች በግልጽ ያስረዳዎታል።
አካውንት ለመክፈት የሚያስፈልጉ ሰነዶች
ለግለሰቦች/ባለሀብቶች አካውንት ለመክፈት በአብዛኛው የሚጠየቁት ሰነዶች የሚከተሉት ናቸው፦
- የታደሰ ሕጋዊ መታወቂያ (ፓስፖርት ወይም ብሔራዊ መታወቂያ)
- የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር (TIN Number)
- የሁሉም አድራሻ እና ስልክ ቁጥር መረጃ
- የባንክ አካውንት ቁጥር (ገንዘብ ለማስተላለፍና ትርፍ ለመቀበል)
- የአካውንት መክፈቻ ቅጽ (Form)
አካውንት ለመክፈት የሚከተሏቸው 5 ቀላል ደረጃዎች
1. ሕጋዊ ብሮከር መምረጥ
በመጀመሪያ በሃገሪቱ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ አካል እውቅናና ፈቃድ የተሰጠውን ብሮከር ይምረጡ። ብሮከሮችን በሚመርጡበት ጊዜ የሚከተሉትን ነገሮች ማወዳደር ተገቢ ነው፦
- የሚጠይቁት የአገልግሎት ክፍያ እና ኮሚሽን መጠን
- የሚያቀርቧቸው የኢንቨስትመንት ዓይነቶች
- የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም (በስልክ መተግበሪያ መስራት መቻላቸው)
- የሚሰጡት የገበያ ጥናትና የምክር አገልግሎት
2. ፎርም መሙላት እና ማመልከት
የመረጡትን ብሮከር የአካውንት መክፈቻ ቅጽ በአካል ወይም ካላቸው በኢንተርኔት በመሙላት ሰነዶችዎን ያያይዙ። ብሮከሩ የእርስዎን ማንነት እና ሕጋዊነት ካረጋገጠ በኋላ አካውንትዎን ይከፍታል።
3. ወደ አካውንትዎ ገንዘብ ማስተላለፍ (Funding)
አካውንቱ መከፈቱ እንደተረጋገጠ፣ አክሲዮን መግዣ የሚሆን ገንዘብ ከመደበኛ የባንክ አካውንትዎ ላይ ወደ አዲሱ የብሮክሬጅ አካውንትዎ በባንክ ዝውውር ያስገቡ።
4. የመጀመሪያውን የገበያ ትዕዛዝ ማስተላለፍ
የገበያ ትዕዛዝ ለማሰተላለፍ ሲፈልጉ ለብሮከርዎ ትዕዛዝ በመስጠት የሚከተሉትን ማድረግ ይችላሉ፦
- የተመረጡ ኩባንያዎችን አክሲዮን መግዛት ወይም መሸጥ
- የመንግሥት ቦንዶችን መግዛት
- አዳዲስ ይፋዊ የአክሲዮን ሽያጮች ላይ መሳተፍ
ትዕዛዝዎን ከመላክዎ በፊት ዋጋውን፣ የክፍያ መጠንን እና የአገልግሎት ክፍያውን ደግመው ያረጋግጡ።
5. ኢንቨስትመንትዎን መከታተል
ብሮከርዎ በየጊዜው ወይም በፈለጉት ሰዓት የእርስዎን የሀብት መጠን የሚያሳይ መግለጫ (Statement) ሊሰጥዎ ይገባል። በዚህ መግለጫ ላይ የትኞቹን አክሲዮኖች እንደያዙ፣ የቀረዎት የገንዘብ መጠን፣ የተደረጉ ዝውውሮች እና የወቅቱ የሀብትዎ ጠቅላላ ዋጋ በግልጽ ይታያል።
ብሮከርዎን ሊጠይቋቸው የሚገቡ ወሳኝ ጥያቄዎች
አካውንት ከመክፈትዎ በፊት እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቀው መረዳትዎን ያረጋግጡ፦
- “ይህንን የኢንቨስትመንት አገልግሎት ለመስጠት ሕጋዊ ፈቃድ አለዎት?”
- “ለእያንዳንዱ ግዢ እና ሽያጭ የሚጠይቁት የኮሚሽን ክፍያ ስንት ነው?”
- “በእርስዎ በኩል ምን ምን ዓይነት የዋስትና ሰነዶችን (አክሲዮን/ቦንድ) መግዛት እችላለሁ?”
- “የግዢና ሽያጭ ትዕዛዝ በስልክ፣ በኢሜይል ወይስ በመተግበሪያ ነው የማስተላልፈው?”
- “አክሲዮን ስሸጥ ገንዘቤ ወደ ባንክ አካውንቴ ለመግባት ስንት ቀን ይፈጃል?”
- “አካውንቴን በድረ-ገጽ ወይም በሞባይል መተግበሪያ መከታተል እችላለሁ?”
ኢንቨስት ማድረግ ከመጀመርዎ በፊት ማወቅ ያለብዎት ነገር፦
የብሮክሬጅ አካውንት መክፈት የገበያውን በር ይከፍትልዎታል እንጂ የኢንቨስትመንት ስጋትን (Risk) አያስቀርም። ማንኛውንም አክሲዮን ወይም ቦንድ ከመግዛትዎ በፊት በምን ላይ ኢንቨስት እያደረጉ እንደሆነ፣ ትርፉ እንዴት እንደሚገኝ፣ ስጋቱ ምን ያህል እንደሆነ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አክሲዮኑን መልሶ ለመሸጥ ምን ያህል ቀላል እንደሆነ አስቀድመው በሚገባ ማጥናት አለብዎት።

